ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም ማዕክል ለመሆን እየሰራች ነው ተባለ

Written by

in

13ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚካሄድ ይሆናል።

​“የማይበገር የጤና ሥርዓትን መገንባት ለምስራቅ አፍሪካ” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ20 በላይ አባል ሀገራት የተወጣጡ ከ2 ሺህ በላይ አመራሮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ኢንቨስተሮችና ፋይናንሰሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

​በጉባኤው ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ፤ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከ580 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርበት ቢሆንም፡ከ70 በመቶ በላይ መድኃኒት እና

​እስከ 99 በመቶ የሚደርሱ ክትባቶችን ከውጭ ሀገር እንደሚያስገባ ገልጸዋል።

​በተጨማሪም በቀጠናው በየዓመቱ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለህክምና ቱሪዝም ወጪ እንደሚደረግ ጠቁመው፣ ይህም ጠንካራ የሀገር ውስጥና የቀጠና የጤና ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ማሳያ ነው ብለዋል።

​እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፣ ጉባኤው የሕክምና አገልግሎት ጥራትን ማረጋገጥ፣ የሜዲካል ቱሪዝምን ማስፋፋት እና የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓቶች ምርትን ማሳደግ ዋና ዓላማዎቹ አድርጎ የተነሳ ነው።

​በተጨማሪም የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን በማጠናከር ዘላቂ የጤና ፋይናንሲንግ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር ዘርፉን ከአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት ጋር ማጣመር የጉባኤው ትኩረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ መደረጉ ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም ማዕክል ለመሆን ለምትስራው ሥራ አጋዥ ነው ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ በኮንፈረንሱ ወቅት በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች የሚፈረሙ ሲሆን፣ ከጉባኤው ጎን ለጎን ለሶስት ቀናት የሚቆይ ነፃ የኤግዚቢሽን መርሃ ግብር ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ገልፀዋል።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ኢንቨስተሮች በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

በ-ናሆም ዮሐንስ

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *